Banner

ቶያች

ቶያች ቀጥተኛ ትርጉሙ ሰፈር ማለት ሲሆን ከዚሁ በተጨማሪ ትርጓሜው የሚያስተላልፈው መልዕክት አለው፡፡ ይኸውም የሐረሪን ባህልና እምነት ፍፁም በሆነ መልኩ ለማቆየት ያስቻለ የአብሮነት ማረጋገጫ አስተዳደራዊ ሥርዓት በባህላዊ ዘዴ መተግበሩን ነው፡፡ በጁገል ክፍለ ከተማ በአርባ ስምንት ሔክታር መሬት አንድ መቶ ሦስት ቶያች ይገኛሉ፡፡

ይህ ባህልን መሠረት ያደረገው ማኅበራዊ አስተዳደር መዋቅር ከጥንታዊቷ ከተማ ፊዚካላዊ አቀማመጥ የበሮቿን አዋሳኝ መሠረት በማድረግ ለአምስት የተከፈለ ሲሆን መጠሪያቸውም በሚያዋስኑት በር ስያሜ ሆኖ አምስቱም ትላልቅ ሰፈሮች በውስጣቸው ብዛት ያለው ንዑሳን ሰፈሮች/ቶያች/ አላቸው፡፡

የንዑሳን ሰፈሮች/ቶያች መጠሪያም በአቅራቢያቸው ባለ ማኅበራዊ ግልጋሎት የሚሰጣቸውና ልዩ በሆነው በአጠቃላይ በነዋሪዎቹ ዘንድ ታዋቂነት ያለው ስም የሚጠሩ ሲሆን ይህ በጥንት ዘመን የነበረና ሲወርድ ሲወራረድ ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር የቆየው ስያሜ ለዛሬው ትውልድ ስለ አካባቢው ለማጥናት ጥንተ ባህል መሠረቱን ዕድገቱን ለማወቅና የነበረውን ሥልጣኔ በሳይንሳዊው ቴክኖሎጂ ለማዳበር ለመነሻ ነጥብነት ግልጋሎት ወደር የሌለው ነው፡፡ በጥንታዊ ከተማ የነበረው የነዋሪዎች ቁጥር ሥርጭትን ለመገመት አስረጂ መነሻ መረጃ ሊሆን ይችላል፡፡
የቶያች ልዩ ባህሪ

1. ሁሉም የየራሳቸው የሆነ ሃሳባዊ ወሰን አላቸው፡፡ ይህንንም ነዋሪዎቹ የየትኛው ቶያች እንደሆኑ ያውቁታል፡፡
2. ኢንፎርማል የሆኑ አባላት አሉት፡፡
3. እያንዳንዱ ቶያ የራሱን ወሰን የሚጠብቅበት ባህላዊ ዘዴ አለው፡፡
4. ነዋሪዎቹ በፈለጉት ቶያ ለመኖር ምንም የሚገድባቸው ነገር የለም፡፡
5. ቶያች ስያሜያቸውን የሚያገኙት በአቅራቢያቸው ከሚያገኙት ነገሮች ሲሆን፤ ይኸውም አዋች፣ መስጂድ፣ ገልማ፣ መጋላ፣ ዑጋ/መንገድ/ እንዲሁም ልዩ ታሪካዊ ቦታዎች . . . የዕውቀት ባለሀብት የሆኑ ግለሰቦች . . . ፣ ከቢሮች፣ ሼኾች፣ ኢማሞች ወዘተ.
ቶያች ያላቸው ጠቀሜታ፤

1. በነዋሪዎቹ መካከል በሚፈጥረው የቅርብ ግንኙነት በመካከላቸው ከፍተኛ መተጋገዝን ፈጥረዋል፡፡
2. ጉርብትናን መሠረት በማድረግ፣ በዝምድና በመተሳሰር፣ በጓደኝነት በመቀራረብና በአፎቻ ማንነትን ጠብቆ ለማኖር ቶያች ቀደምት ዘዴዎች ናቸው፡፡
3. በነዋሪዎቹ ላይ ከፍተኛ የሆነ የራስ የመተማመን ስነ-ልቦና አጎልብቶአል፡፡
(መፍቱህ ዘካሪያ አብዱላሂ ኑር፤ ሐረር-ጁገል፣ 2000)