በቀጣይ አምስት አመታት መልካም አስተዳደር እንዲሰፍንና የልማት ማነቆ የሆኑትን ጥገኝነትና....
Last Updated on Sunday, 18 July 2010 08:21 Written by Admin1 Sunday, 18 July 2010 08:16
Spurce Harari Mass Media
በቀጣይ አምስት አመታት መልካም አስተዳደር እንዲሰፍንና የልማት ማነቆ የሆኑትን ጥገኝነትና ሙሰኝነትን ለማስወገድ በሁሉም ዘርፍ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ እቅድ በመንደፍ ለተግባራዊነቱ መዘጋጀቱን የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ አስታወቀ፡፡
የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ ማዕከላዊ ጽ/ቤት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ተነጋግሮ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡
የሐብሊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በተከታይ ቀናት ያካሄደውን ስብሰባ አስመልክቶ የሐብሊ የድርጅት ጉዳይ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ያሲን ሁሴን ሸሪፍ በተለይ ለሐረሪ ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሊጉ የተጀመረውን ግምገማ በማጠናከርና የግምገማ ስርዓትን በመዘርጋት ሥራ የማያሰሩ አመራሮችና ጎታች አሰራሮችን ለማረምና ለማስተካከል የሚወስደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡
በመሬት አስተዳደር ስርዓቱ የታየው ቁልፍ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንም የሆነውን ሙስናና ጥገኝነት ለመዋጋት ሊጉ የጀመረውን የማጥራት ሂደት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ማስረገጡን የገለፁት አቶ ያሲን የሚያስፈፅመውን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ልማታዊ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የመሬት አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋት ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት መረባረብ እንደሚያስፈልግ በጉልህ ያሰመረበት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የሐብሊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በተለይም የሐረር ህዳሴን በተመለከተ በስራው ተነጋግሯል፡፡
የህዳሴውን መርሃ ግብር ለማሳካት የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል በሀገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙ ወዳጆች ጋር በመተባበር ቅርሶች ለልማት እንዲውሉና እንዳለሙ ለማድረግ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቅቆ ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመዋል፡፡ የሐረር ህዳሴን ፅንሰ ሐሳብ በተመለከተም በሚገባ ሊታወቅ እንደሚገባ የሥ አስፈፃሚ ኮሚቴው ባደረገው ጥልቅ ውይይት የህዳሴው መሰረታዊ ተግባር የህዝብን አመለካከት ባህሪይ የመለወጥ ተግባር መሆኑን በማስረዳት ለተግባራዊነቱ ህብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ጥሪ ማስተላለፉን አቶ ያሲን ሁሴን ሸሪፍ የሐብሊ ማዕከላዊ ጽ/ቤት የድርጅት ጉዳይ ዘርፍ ሃላፊ ከሰጡት ድርጅታዊ መግለጫ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የሐብሊ ማዕከላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባውን በዚህ ሳምንት ውስጥ እንደሚካሄድ ጽ/ቤቱ የገለፀ ሲሆን የተለያዩ ውሳኔዎችን እንደሚያስተላልፍ ይጠበቃል፡፡















